ከሀዲይ ነፈራ ቅርምት ጀርባ ያለው እውነታ ሲገለጥ – የHMN ምርመራ ዉጤት

Land Grab in Hadiya Ethiopia

የሀዲይ ነፈራ/ ጀሎ ደቀዬ/ ጎፈር ሜዳ ጉዳይ ሰሞኑን መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ በ15/08/2012 ዓ.ም የሆሳዕና ከተማ አስተዳደሩ ከሀዲያ ዞን ጋር በመሆን ሀዲይ ነፈራን ለፖለቲከኞች፣ ለዳኞች፣ ለዶክተሮች መከፋፈል ይጀምራል፡፡ መሬቱ መከፋፈል መጀመሩ አብዛኛውን ህዝብ አስቆጥቷል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ቁጣውን ዋጥ አድርጎ የዞኑን እና የከተማ አስተዳደሩን የማንአለብኝነት እንቅስቃሴ በቸልታ አይቶ አላለፈም፡፡ መሬቱ ለግለሰቦች እየተከፋፈለ መሆኑን የሚገልጹ ዜናዎች በማህበራዊ ሚዲያ መዘዋወር ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ መላው የሀዲያ ህዝብ በተለያዩ መንገዶች ቁጣውን ሲገልጽ ሰንብቷል፡፡ አንዳንዶቹ ቅሬታቸውን ይዘው በአካል እስከ ክልል ሄደዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች “እኛ እያለን ሜዳው አይነካም” ብለው ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸው አረጋግጠናል፡፡

“““““`
የሀዲያ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ መነቃቀነቅ የሀዲያ ዞን እና የዋቻሞ/ሆሳዕና ከተማ አመራሮችን አስደንግጧቸዋል፡፡ መሬቱ አልተከፋፈለም በማለት ህዝቡን ለማዘናጋት ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል፡፡ የዋቻሞ (ሆሳዕና) ከተማ አስተዳደር በሰጠው መግለጫ ሀዲይ ነፈራ/ ጎፈር ሜዳ ለዶክተሮችና ለዳኞች ስለመከፋፈል በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው መረጃ “የሀሰት መረጃ ነው” ሲል ለማስተባበል ሞክሯል፡፡ ከሀዲይ ነፈራ ውጭ የሆነ 4 ሺ 700 ካሬ ሜትር መሬት በህብረት ስራ ማህበር ከለተደራጁ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉት ከመከፋፈል ውጪ የጎፈር ሜዳን አካል ለዳኞችም ሆነ ለዶክተሮች አለመስጠቱን በሰጠው መግለጫ ለማስተባበል ሞክሯል፡፡

“““““
ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው መግለጫ ብዙዎችን አላሳመነም፡፡ ለዘመናት ተከብሮ የኖረው የከተማ ሳንባ የሆነው መሬት በመሸንሸኑ የተነሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ ተብሎ የተሰጠ መግለጫ እንጂ እውነታው ይህ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ የሀዲያ ሚዲያ ኔት ወርክ የሀዲያ ዞን የመሬት ልማት ባለሙያዎችን እና የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎችን ስለ ጉዳዩ አናግሮ እውነታውን አጣርቷል፡፡

የጠየቅናቸዉ መመለስ ያለባቸዉ ጥያቄዎች

“““““`
እውነትም በሀዲይ ነፈራ ለፖለቲከኞች፣ ዳኞችና ዶክተሮች እየተከፋፈለ ነው? መሬት እየተሰጠ ያለው አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች ወይስ አቅም ላላቸውና ከዚህ ቀደም መሬትና ቤት ላላቸው? ዓለም በሙሉ የጋራ ጠላት በሆነው ኮሮናቫይረስ ላይ በአንድነት እየዘመተ ባለበት በዚህ ወቅት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር እና የሀዲያ ዞን ለምን መሬት ለመሸንሸን ተነሱ? የመሬት ልማት እና የማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ለዚህ መልስ አላቸው፡፡

“ ‘ሀዲይ ነፈራ/ ጎፈር ሜዳ ለዳኞችና ለዶክተሮች አልተሸነሸነም ብሎ’ ያወጠው መግለጫ ነጭ ውሸት ነው፡፡”

“““““`
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የሀዲያ ዞን የመሬት ልማት ከፍተኛ ባለሙያ እንደተናገሩት፤ የከተማ አስተዳደሩ “ሀዲይ ነፈራ/ ጎፈር ሜዳ ለዳኞችና ለዶክተሮች አልተሸነሸነም ብሎ” ያወጠው መግለጫ ነጭ ውሸት ነው፡፡ በእርግጥ መሬቱ እየተከፋፈለ ያለው ለዳኞችና ለዶክተሮች ብቻ አይደለም፡፡ ከባለሙያዎች እውቅና ውጭ በሆነ መንገድ በፖለቲከኞች ውሳኔ ብቻ፤ የመሬት አሸናሸን መስፈርቶችን ባላሟላ መልኩ ለዘመናት ተከብሮ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረው ሀዲይ ነፈራ ለሁለት የአመራር ማህበራት፣ (የዞን እና የሆሳዕና ከተማ አመራር ማህበራት) ለሁለት የሆስፒታል ዶክተሮች ማህበራት እና ሁለት ለሁለት የዳኞች ማህበራት፤ በአጠቃላይ ለስድስት ማህበራት የመከፋፈል ስራው ተጀምሮ ነበር፡፡

“““““`
ለዳኞች ለአመራሮች እና ለዶክተሮች እየተሸነሸነ ያለው ቦታ ለህዝብ ላይብረሪ፣ ለመንገድ እና አረንጓዴ ቦታነት የተለዩ ናቸው የሚሉት ባለሙያው፤ በመጀመሪያ ለቤተ መጽሃፍት የተቀመጠውን መሬት ብቻ ለመከፋፈል የታሰበ ቢሆንም በስድስት ማህበራት ተደራጅተው መሬት ለመውሰድ ለቀረቡት ለዳኞች፣ ለፖለቲከኞችና ለዶክተሮች መሬቱ በቂ ባለመሆኑ ለመንገድና ለአረንጓዴ ቦታነት የተቀመጠው መሬት ጭምር እየተሸነሸነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“““““`
እኝህ ባለሙያ እንደሚሉት መሬቱን ለመውሰድ ከተደራጁት የከተማ እና የዞን አመራሮች ውስጥ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ፣ የሀዲያ ዞን ከተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ተስፋሁን እና የሆሳዕና ከተማ ከንቲባ አቶ ታምራት ግዘው ይገኙበታል፡፡ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የዞኑ እና የከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እና የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ይገኙበታል፡፡
በከተሞች ፕላን ህግ መሰረት ለአረንጓዴ ቦታነት እና ለመንገድ ተብሎ የተቀመጠ ቦታ በፕላኑ መሰረት ለታሰበለት ዓላማ መዋል አለበት፡፡ ይህን ፕላን መቀየር አይቻልም፡፡ ተቀይሮ ከተገኘም ከባድ ወንጀል ነው፡፡ የሀዲያ ዞን እና የሆሳዕና ከተማ አመራር ግን በመመሳጠር ለአረንጓዴ ቦታ፣ ለቤተ መጽሃፊት እና ለመንገድ የተባለውን መሬት ፕላኑን በመቀየር የመኖሪያ ቤት በሚለው ተክተው ለራሳቸው እየተከፋፈሉት ነው፡፡ ፕላኑን ዞንና ከተማ አስተዳደር ውስጥ ከመቀየር አልፎ እስከ ክልል በመሄድ የአካባቢውን አዲስ ፕላን አዘጋጅተዋል፡፡ ይህም የሆነው ለህዝብ ወይም ለከተማዋ ታስቦ ሳይሆን የጥቂቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው፡፡

“““““`
የከተማዋ ነዋሪ መሬት ለዶክተሮች፣ ለዳኞች ወይም ለአመራሮች ለምን መሬት ተሰጣቸው የሚል የቅናት ሀሳብ የለውም፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም መሬት ወስደው ቤት ሰርተው እየኖሩ ያሉ ግለሰቦች ተጨማሪ መሬት እየወሰዱ በመሆናቸው ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት የከተማ ልማት ዘርፍ ባለሙያው እንደሚሉት፤ አሁን መሬት እየወሰዱ ያሉ ፖለቲከኞች መንግስት በሰጣቸው ቤት ውስጥ ሚኖሩ ናቸው፡፡ ዳኞችም እንዲሁ ሪል ስቴት ውስጥ ያሉ ሲሆኑ የንግስት እሌኒ ሞሃመድ ሆስፒታል ዶክተሮች ደግሞ ዋቻሞ ዩንቨርሲቲ ቤት ሰጥቷቸው የሚኖሩ ናቸው፡፡
አብዛኞቹ ዳኞች የዳኝነት ስልጣናቸውን በመጠቀም በከተማዋ በርካታ ቦታዎች ላይ ከዚህ ቀደም መሬት ወስደዋል፡፡ የወሰዱትን መሬት ግን በስማቸው አያስቀምጡም፡፡ በአፋጣኝ በእህት እና በወንድም ስም ቀይረው ሌላ መሬት ለመውሰድ ተደራጅተው ይመጣሉ፡፡ ግማሹ ሸጦ ነው ተመልሶ እየመጠ ያለው፡፡ ከእነዚህ ዳኞች መካከል የተወሰኑትን በስም መጥቀስ ይቻላል፡፡

“““““`
ለምሳሌ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አቶ ተስፋሁን እና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ውስጥ የሚሰራው አቶ ኤርሲዶ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አቶ ተስፋሁን በሪል ስቴት ቤት አለው፡፡ ኤርሲዶ ደግሞ ከዚህ ቀደም መሬት ወስዶ በመሬቱ ጉዳይ ከባለቤቱ ጋር ተጣልቶ መሬቱን ሸጧል፡፡ እነዚህ ሁለቱም ግለቦች አሁን በማህበር ተደራጅተው ከሀዲይ ነፈራ መሬት ለመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ካሉት መካከል መሆናቸው የመረጃ ምንጫችን አረጋግጠዋል፡፡
የዞንና የከተማ አመራር ደግሞ በመንግስት ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ መንግስት በሰጠው ቁጠባ ቤት እየኖሩ ግን ተደራጅተው ጎፈር ሜዳን እየተከፋፈሉ ነው፡፡ የቤቶች ማህበር አደረጃጀት ደንብ መሰረት አንድ ግለሰብ በመንግስት ቤት ውስጥ እየኖረ ተጨማሪ መሬት መውሰድ ወንጀል እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

“““““`
የመረጃ ምንጫችን እንደሚሉት፤ የሆሳዕና እሌኒ ሞሃመድ ሆስፒታል በዋቻሞ ዩንቨርሲቲ ስር ስለሆነ የዋቻሞ ዩንቨርሲቲ ለዶክተሮቹ መኖሪያ ቤት ሰጥቷቸዋል፡፡ ቤት ላልደረሳቸው ደግሞ ዩንቨርሲቲው ቤት ገዝቶ እየሰጣቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ሆስፒታሉ የዩንቨርሲተው አካል ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ለባለሙያዎች ቤት ሰርቶ የማቅረብ ሀላፊነት ቤት በመስጠት ሀላፊነቱንም እየተወጣ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ በማህበር ተደራጅቶ መሬት መውሰድ ህገ ወጥ ነው፡፡

“““““`
የሆሳዕና ከተማ የማህበራት አደረጃጀት በጣም ችግር ያለበት መሆኑ አሁን ለተፈጠረው ችግር አንድ መንስኤ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ አደረጃጀቱ መሬት ያለው ሰው ተመልሶ በሌላ ሰው ስም ቀይሮ ነው ተደራጅቶ እንዲወስድ በር የሚከፍት ነው፡፡ በህጉ መሰረት ሰዎች መሬት ለመውሰድ በማህበር መደራጀት ያለባቸው ከዚህ ቀደም ከመንግስት መሬት ስለመውሰዳቸው እና ስላለመውሰዳቸው በማዘጋጃ ቤት ተጣርቶ ነው፡፡ አሁን ግን ማዘጋጃ ቤት ማን የት መሬት አለው የሚለውን ሳያጣራ ነው የዞኑ ህብረት ስራ ማህበር ሰዎችን እያደራጀ ያለው፡፡ አሁን የተደራጁት፣ የዳኞች፣ የዶክተሮች እና የከተማና የዞን አመራር ማህበራት በማዘጋጃ ቤት አይታወቅም፡፡

“““““`
አብዛኞቹ የማዘጋጃ ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች ራሳቸው ችግር ያለባቸው በመሆኑ አመራሮች፣ ዳኞችና ዶክተሮች ከዚህ ቀደም መሬት እንዳላቸው እያወቁ ጭምር የላቸውም ብለው ማስረጃ የሚሰጡበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አብዛኛው የማዘጋጃ ቤት አመራር እና ባለሙያ በመሬት ቅርምት ውስጥ እጁ አለበት፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች በተለይም የዳኞችን ፊት ቀና ብለው ለማየት ይፈራሉ፡፡ በየቦታው መሬት ሲዘርፉ እና ካርታ ላይ ካርታ ሲሰሩ የኖሩ ወንጀለኞች አሉ፡፡ እነዚህ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቢቀርቡ ብዙ ሊያስቀጣቸው ይችላሉ፡፡ ዳኞች ብዙ እንዳይቀጧቸው በተለይም ዳኞች እና አመራሮች ማዘጋጃ ቤት ለመጠየቅ ሲመጡ ዳኞቹ እና ፖለቲከኞቹ ቤት እና መሬት እንዳላቸው እያወቁ መሬት የላቸውም እያሉ ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡

“““““`
ዳኞችም ለዚህ ውለታ ደግሞ ወንጀለኛ የማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎችንና አመራሮች በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በነጻ እንዲለቀቁ ያደርጋሉ በመሆኑም አሁን ዳኞችን ማንም አይጠይቃቸውም፡፡ መሬት ዘረፋውን እያጧጧፉ ያሉት እነሱ ናቸው፡፡ ማንም አይጠይቃቸውም፡፡
በመሆኑም መሬት ያላቸው ሰዎች ተጨማሪ እንዲወስዱ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አዲስ መሬት ለመውሰድ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን መሬት ሸጠው አዲስ እንዲወስዱ እንዲሁም በባል ስም መሬት ወስደው ከሆነ በቀጣይ በሚስት ስም፣ በልጅ ስም እየተደራጁ፣ በወንድም፣ በእህት፣ በአጎት ስም መሬት እንዲቀራመቱ ምቹ ሆኖላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማዋ መሬት መሬት ለሌላቸው ሳይሆን መሬት ላላቸው በድጋሚ እየተከፋፈለ ነው፡፡

“““““`
እንደ ምንጫችን ማብራሪያ፤ ቀድመው የተመዘገቡ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የተደራጁበት ከ200 በላይ ማህበራት መሬት ጠይቀው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ አብዛኛው አመራር፣ ዳኛ እና ዶክተሮች ግን መሬት ላይ መሬት ለመደረብ ያለወረፋቸው ነው በመውሰድ ላይ ያሉት፡፡
ለብዙ ዓመታት ወረፋቸውን ሲጠባበቁ የነበሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች መሬት ሳያገኙ፤ በቅርቡ ከወረዳዎች የመጡ አመራሮች በመንግስት ቤት ላይ ተጨማሪ መሬት እየተሰጣቸው ነው የሚሉት የመረጃ ምንጫችን፤ አንዳንዶቹ ከተሸሙ ዓመት እንኳ ያልሞላቸው በቅርቡ ከወረዳ የመጡ ናቸው ለአብነት ያህል አሁን ተደራጅተው መሬት እየወሰዱ ካሉት ውስጥ በድርጅት ማዕከል ላይ ከተሸሙ ዓመት እንኳ ያልሞላቸው አቶ ደስታ ተስፋዬ ዋቻሞ (ሆሳዕና) ከገቡ ዓመት አይሆናቸውም፡፡

መሬቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና ለተደራጁት ማህበራት ነው እየተሰጠ ያለው የሚለው የከተማ አስተዳደሩ መግለጫ ከእውነታ የራቀ ነው

“““““`
የብልጽግና ፓርቲ የከተማ ፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ደግሞ ከወረዳ ሆሳዕና ከገቡ ገና ሶስት ወራቸው ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መሬት እየተሰጣቸው ያሉት የብልጽግና ፓርቲ አመራር ስለሆኑ ነው፡፡
መሬቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና ለተደራጁት ማህበራት ነው እየተሰጠ ያለው የሚለው የከተማ አስተዳደሩ መግለጫ ከእውነታ የራቀ ነው፡፡ በከተማዋ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሬት አግኝቶ አያውቅም፡፡ ተደራጅተው ጥያቄ አቅርበው አራትና አምስት ዓመት ሲጠብቁ የኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በከተማዋ የፈለገውን ቦታ እየወሰደ ያለው የፖለቲካ አመራሩ ነው፡፡

“““““`
ዓለም በጭንቀት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ሀዲይ ነፈራን መቀራመት ለምን አስፈለገ? እንደሚታወቀው የሀዲያ አካባቢ በአሁኑ ወቅት በሁለት ኮማንድ ፖስት ነው እየተመራ ያለው፡፡ በአንድ በኩል የሀዲያን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን የደቡብ ክልል ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አለ፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል መንግስት ኮሮናን ለመከላከል ያወጀው ኮማንድ ፖስት አለ፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ህዝቡ ጥያቄ እንዳያነሳ እና ቅሬታው እንዳያሰማ ኅዝቡ በፍርሃት ተሸብቧል፡፡

“““““`
በህጉ መሰረት ግን ህዝብ አመራሩን በየሶስት ወሩ መተቸት እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ድሮው ህዝቡ ተሰብስቦ ፐብሊክ ሂሪንግ ተብሎ ህዝቡ በየሶስት ወሩ ችግሩን የሚገልጽበት ሁኔታ የለም፡፡ አስተያየት መስጫ ጊዜ የለም፤ ስብሰባዎች ተከልክለዋል፡፡ ግለሰቦች እንደግለሰብ ይህ ለምን እንዲህ ይሆናል ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ ከሆነ ደግሞ የክልሉን ኮማንድ ፖስት ወይም የፌዴራሉን የኮማንድ ፖስት መመሪያ በመተላለፍ በሚል እስር ቤት ለመወርወር ምቹ ነው፡፡

“““““`
በመሆኑም ይህን አጋጣሚ መጠቀም የህዝብ መሬት ለመሸንሸን ለአመራሩ የተሻለ አመራጭ ነው፡፡
የሀዲያ ዞን እና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር መሬት ቅርምት ላይ እንዲያተኩር ያደረገው ምክንያት ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከዞን እስከ ቀበሌ የሚገኝ አመራር ከስልጣን እነሳለሁ የሚል ስጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ አመራሩና ህዝቡ መካከል መግባባት የለም፡፡ የበርካታ ወረዳዎች እና ከተማ ህዝብ ተደራጅቶ ክልል እና ፌዴራል ድረስ በመሄድ አመራሩ ችግር ስላለበት ይነሳልን የሚል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መንግስት አመራሮችን ለማንሳት እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሮና ቫይረስ ጣልቃ በመግባቱ መንግስት ሊወስድ ያሰበውን እርምጃ አስተጓጎለው፡፡ ኮሮና በቁጥጥር ስር ሲውል እነዚህ አመራሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ስለገመቱ ከመነሳታቸው በፊት የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመን መሬት መቀራመት አለብን የሚል ሩጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡

“““““`
የከተማው አስተዳደር ሀዲይ ነፈራን አልነካሁም ብሎ በተደጋጋሚ ቢምልም በተግባር ግን ሀዲይ ነፈራ መሸንሸን ከተጀመረ ሰንብቷል፡፡ እንደ አሁኑ ለዳኛና ለዶክተር በሚል ባይሆንም ከዚህ ቀደምም ለሀይማኖት ተቋማት በሚል ሜዳውን መቸብቸብ ተጀምሮ ነበር፡፡ በተለይም ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ለዘመናት ሳይደፈር ቆየው የሀዲይ ነፈራ እየተደፈረ ነው፡፡ ለመልካም ወጣት ማዕከል መገንቢያ በሚል ለዮናታን 100 ሺህ ካሬ እና ለኦርቶዶክስ የጥምቀት እና የደመራ ማክበሪያ በሚል ደግሞ 20 ሺህ ካሬ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሁለቱም ህገ ወጥ ናቸው፡፡ የመረጃ ምንጫችን እንደሚሉት ለአገልጋይ ዮናታንም ሆነ ለኦርቶዶክስ የተሰጠው መሬት ህግንና ደንብን የጣሰ ነው፡፡

“““““`
በ2008 በወጣው ደንብ መሰረት ግሪን ኤሪያዎች ለማንም ተላልፎ መሰጠት እንዳሌለበት ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የመሬት ሊዝ አዋጅ እና የቀብር እና የአምልኮ ቦታ አሰጣጥ አዋጅ የሚጻረር ነው፡፡

“““““`
ለአገልጋይ ዮናታን ለመስጠት የታሰበው መሬት እና የእሱ ፍላጎት ስላልተጣጣመ እንዲሁም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞዎች ስለበረቱ ለአገልጋይ ዮናታን የተሰጠው መሬት ወደ ሌላ ቦታ እንዲቀየር ተደርጓል፡፡ ለኦርቶዶክስ በአመት ሁለት ቀን ለሚከበር በዓል የተሰጠው መሬት ግን አሁንም የጭቅጭቅና የንትርክ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ አልተሳካላቸዉም እንጂ ሥራቸዉ ሀዲያ ዉስጥ አላስፈላጊ የሃይማኖት ክፍፍልን ሊያመጣ ይችል ነበር። ዋናዉ የችግሩ መንስኤ ባለስልጣናት ለሃይማኖት ድርጅቶች የህብን መሬት ልክ እንዳባታቸዉ ርስት ማከፋፈል መጀመራቸዉ ነዉ። በዛ ዕለት ነዉ ጥንስሱ የተጣለዉ።

“““““`
አሁንም የመሬት ቅርምቱ የቆመው የከተማው ህዝብ በተለይም ወጣቱ ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል ለጊዜው ማስቆም ተችሏል፡፡ ሁሉም የከተማው ህዝብ ሀዲይ ነፈራን ለመሸንሸን መጀመሩን ሲሰማ ብርቱ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡

ህዝቡ በሌቦች ላይ የጀመረውን ትግል መቀጠል አለበት

“““““`
ባለሙያው እንደሚሉት ህዝቡ በሌቦች ላይ የጀመረውን ትግል መቀጠል አለበት፡፡ በእንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ የሚሰማሩትን መታገል አለበት ዘመድ እንኳ ቢሆን እንደ ዘመድ አይቶ መተው የለበትም፡፡ የህዝብ ቤተመጽሃፍት የሚገነባበትን እና ለአረንጓዴ ቦታነት የተተወውን መሬት የሚከፋፈል ማንም ይሁን ማን ህዝቡ ማውገዝ እና ለህግ እንዲቀርብ ጫና ማሳደር አለበት፡፡

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *